በ1990 ዓ.ም ነበር፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት አመራሮች የነበርነው እኔ፣ አሰግድ ወርቃለማሁ እና ጌታነህ ይስማው ወደ ጎንደር፣ ዓለማያ፣ ባህር ዳር እና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች በመሄድ ነፃ የተማሪዎች መማክርቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ የመላ ኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረትን ለማቋቋም መሰረት በመጣል ላይ ነበርን፡፡ መቼም ያኔ በመላ ሀገሪቱ የነበረው ተማሪዎች አንድነትና ራዕይ ልዩ ነበር፡፡ የዩኒቨርስቲው አመራር ጉዟችንን ቢቃወምም የተጓዝነው በራሳችን ህብረት ባጀት ነበር…
lkj32
ከተልዕኳችን ስንመለስ በሳምንታት ውስጥ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አመፅ ተቀስቅሶ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ወደ ግቢው ገብተው በተማሪዎች ላይ ከባድ ድብደባ ፈፀሙ፡፡ እኛው በታዛቢነት ቁመን በመላ ተማሪው ያስመረጥናቸው አምስት የተማሪው አመራሮች በአመፁ እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው በአያሌው ጎበዜ ፊርማ (በወቅቱ የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ነበር) ከትምህርት ገበታቸው እንዲባረሩ ተደረገ፡፡ ልጆቹ ግን በአመፁ ጊዜ አመፁን ህጋዊ መስመር ለማስያዝና ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል ተሰብስበው እየመከሩ እንጂ አመፅ እያደራጁ አልነበረም፡፡ እነዚያ ምስኪን ልጆች ለመጓጓዣ ከጓደኞቻቸው ለምነው በቀጥታ ወደ እኛው ግቢ ስድስት ኪሎ መጡ፡፡ “ለትምህርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ገነት ዘውዴ አቤት በሉልን” አሉ፡፡
በስድስት ኪሎ ግቢ መኝታና ምግብ እንዲያገኙ አስድርገን በሚቀጥለው ጧት እኔና አሰግድ ወደ ሚንስትሯ ቢሮ ቁልቁል በረርን፡፡ ትንሽ ከተወያየን በኋላ አሰግድ እንዲህ አላት፤ “አሁን ያለሽን ብቸኛ ተስፋ አንቺ ነሽ፤ ውሳኔው በድሃይቱ ሃገርና በድሃዎቹ ወላጆቻቸው ላይ ከባድ ኪሳራ የሚያስከትል፣ አሳፋሪና የአካዳሚክና የመደራጀት መብትን አፈር ድሜ ያስጋጠ ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀልብሽልን፡፡”
“እንደ ትምህርት ሚንስትርነቴ በክልሉ መንግስት ውሳኔ ውስጥ ጣልቃ መግባት አልችልም። ቢሆንም ግን እንደ ብአዴን አባልነቴ አያሌው ጓዴ ስለሆነ ውሳኔውን እንዲቀይር እለምነዋለሁ” ብላ ስልክ ለመደወል ተነሳች፡፡ “እባክህ አያሌው ውሳኔህን እንደገና እይላቸው፤ መቼስ ምን ይደረግ፤ ወጣቶች አይደሉ? እኛም እኮ ተማሪ እያለን እንረብሽ ነበር… ይኸው ከስድስት ኪሎ የመጡ ሁለት ልጆች ውሳኔውን ካላስቀየርሽ ከቢሮሽ አንወጣም ብለውኝ እኮ ነው…” መቼም እያዋዛች ማግባባት ትችልበታለች፡፡ (ሚንስትሯን ትንሽ ቀረብ ብዬ ስለማውቃት የምታገለግለው መንግስት ወለፈንድ ሆኖባት እንጂ ከተማሪ ጋር በቀላሉ መግባባት አያቅታትም ነበር፤ ተማሪን/ወጣትን የመረዳት ችሎታና ፍላጎቱ ነበራት፡፡)
ያም ሆነ ይህ ግትሩ አያሌው በውሳኔው ፀና፡፡ እንደገና እንደምትለምነው ነግራን በሚቀጥለው ጧት እንድንመለስ ነገረችን፡፡ ሰውዬው የጠላት ሀገር ዜጋ ከሀገር ያባረረ ይመስል አቋሙን ሳይቀይር ቀረ፡፡ የገበሬ ልጅ የሆነው “ገበሬው” አያሌው በገበሬ ገንዘብ፣ የገበሬ ሀገር በሆነችው ሀገር ጥሪት በሚማሩ የገበሬ ልጆች ላይ ያልተማረ ገበሬ እንኳን የማይወስነውን አርቆ አሳቢነት የጎደለው ውሳኔ በማሳለፍ ተማሪዎቹ እንደገና ተመልሰው ገበሬ እንዲሆኑ ፈረደባቸው፡፡ ከ18 ዓመታት በኋላ በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆኖ እነዚያ ተማሪዎች ሊቀመጡበት በሚገባቸው ቦታ ላይ ተቀምጦ የጡረታ ዕድሜውን ይገፋል፡፡ አይ ኢትዮጵያ! ምፀት የበዛብሽ የጉድ ሀገር!
በሰሞኑ አመፅ ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ከየዩኒቨርስቲዎች ከትምህርት ገበታቸው እየተባረሩ መሆኑን እሰማለሁ፡፡ አንዳንዶች ማስታወቂያዎች እንዲያውም ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ይታገዱ ወይስ ለዘላለሙ ይባረሩ ግልፅ አይደሉም፡፡ በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ማሰናበት ግለሰብን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን፣ ሀገርን… ምን ያህል መራራ ዋጋ እንደሚያስከፍል እስኪ አስሉት… አይ የድሃ ልጆች አበሳ! አይ የድሃ ቤተሰቦች እንባ! አይ የዚህች የጉድ ሀገር መከራ! ፍፁማዊ አገዛዝ የነበራቸው አፄ ኃይለ ስላሴ እኮ ተማሪ ዙፋኔን ተዳፈረ፣ እንቁላልና ስጋ እየቀለብኩት አመፀብኝ… ብለው ተማሪ አባረው አያውቁም… የደርግ ባህሪም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነበር! ጥፋት ቢያጠፉ እንኳን ተግሳፅ ተሰጥቷቸው ይስተካከላሉ እንጂ እንዴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው በጅምላ ይባረራሉ…? የት እንዲሄዱ ነው የሚባረሩት…? ዩኒቨርስቲዎቸ እኮ የሰፊው ድሃ ገበሬ ንብረቶች ናቸው…

ከትምህርታቸው በመባረር ላይ ያሉትን ተማሪዎች አስቧቸው!(ቻላቸው ታደሰ)

| Uncategorized |
About The Author
-