alk
በቅርቡ ለቻን የእግር ኳስ ውድድር ዘገባ ወደ ርዋንዳ የተጓዘው ጋዜጠኛ ወዳጃችን አወቀ አብርሀም በነበረበት ቡታሬ ከተማ የቴዲ አፍሮ “ላምባዲና” ሙዚቃ በጣም ተወዳጅ መሆኑን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቦን ነበር፡፡ እኔም ከሰሞኑ የኬንያ ጉዞዬ የአወቀን መረጃ ትክክለኛነት ያረጋገጠልኝ አጋጣሚ ነበረኝ፡፡
ጃከስ ፉራሀ በርዋንዳ በኪጋሊ ዴይሊ የራደዮ ጣቢያ ነው የሚሰራው፡፡ ናይሮቢ ላይ ስንተዋወቅ ከኢትዮጵያ መሆኔን ሲያውቅ አስቀድሞ ያወራኝ ቴዲ አፍሮ ላምባዲና ሙዚቃ ተወዳጅነት ነበር፡፡ በሚሰራበት የራዲዮ ጣቢያ በዲጄዎች ከሚጫወቱ የአፍሪካ ሙዚቃዎች መካከል ላምባዲና አንዱ መሆኑን ነገረኝ፡፡ በኪጋሊ የምሽት መዝናኛ ቤቶችም እንደሚሰማ….የሙዚቃው ቪዲዮ ምስልም (ክሊፕ) በሀገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ይቀርባል አለኝ፡፡
ቋንቋና ትርጉሙን ባያውቁትም ሙዚቃውን የሚዘፍኑ ብዙ ርዋንዳውያን መኖራቸውን ነገረኝ፡፡ ራሱም በጥቂቱ አንጎራጎረልኝ፡፡ ትርጉሙን ስነግረውም ይበልጥ ተደነቀ፡፡ በተደጋጋሚም “Wow! What A Music!” ይል ነበር፡፡
“ሙዚቃ እንዲህ ግዙፍ መልዕክት ሲሸከም ይበልጥ ደስ ይላል፡፡ ሰዎችን የመግዛት ሀይል ይኖረዋል” ሲልም አድናቆቱን ገለጸ፡፡ እኔም ከላምባዲና የበለጠ ግዙፍ ሀሳብ ያላቸው የቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች መኖራቸውን በመንገር እንዲሰማቸው ጠቆምኩት፡፡ ለጊዜው የምሰማቸውን የቴዲና ሌሎች የሀገሬን ምርጥ ሙዚቃዎችንም ሰጠሁት፡፡ በጣም ደስ አለው፡፡ “ኪጋሊ ገብቼ የጣቢያችን ዲጄዎች ላይ ጉራዬን ለመንፋት ቸኩያለሁ” ብሎኛል፡፡
ርዋንዳዊው ጋዜጠኛ ፉራሀ ወደ አዲስ አበባ ልመለስ ሲሰናበተኝ እንዲህ ይህን አደራ በመስጠት ነበር፡፡ “ቴዲ አፍሮ እኛ ጋ በጣም ብዙ አድናቂ አለው፡፡ እባክሽን ኪጋሊ ላይ ኮንሰርት እንዲያዘጋጅ ንገሪልኝ’’
በጉዞዬ የተዋወኳቸው ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ቴዲ አፍሮን ያውቁታል፡፡ ከሙዚቃው ይበልጥም ዜና የሆነባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በደንብ ያውቃሉ፡፡ ሙዚቀኞቻችን ከሀገራቸው ውጪ ባሉ የአፍሪካ ከተሞች ለመደመጥ ሙዚቃዎቻቸውን ለራዲዮ ጣቢያዎችና ለዲጄዎች መስጠት፣ ከአፍሪካ ሙዚቀኞች ጋር በጋራ መስራት፣ ደረጃውን የጠበቀ የቪዲዮ ክሊፕ ለቴሌቭዥን ጣቢያዎች መላክ እንደሚጠበቅባቸውም ተረድቻለሁ፡፡
.
“ላምባዲና” በርዋንዳ ብቻ ሳይሆን በኬንያ በናይሮቢም በምሽት ቤቶች ይሰማል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ባርና ሬስቶራንቶች ላይደንቅ ይችላል፡፡ ከናይሮቢ 150 ኪ∕ሜ ርቃ በምትገኘው ናይቫሻ ላይ ሙዚቃውን የሚያጫውት ዲጄ ማግኘቴ ግን እኔን ደንቆኛል፡፡
ዲጄ ኤም ናይቫሺያ ባረፍንበት በሲስንስ ሆቴልና ላውንጅ የምሽት ሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) ነው፡፡ ዘወትር ምሽት የብዙ አፍሪካ ሀገሮች ሙዚቃን ሲያጫውት እሰማለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ግን አልሰማሁም ነበርና ድንገት ስተዋወቀው የሀገሬን ሙዚቃ ለምን እንደማያጫውት ጠየኩት፡፡ “አልሰማሽ ይሆናል እንጂ አጫውታለሁ፡፡ የሀበሻ ጓደኞቼ ሙዚቃቸውን ይሰጡኛል” አለኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞችም የዲቦ፣ (ማንአልሞሽ ዲቦን ማለቱ ነው) ቴዲ አፍሮ፣ አስቴር አወቀ፣ ናቲ ማን፣ ሀይሌ ሩትስ ሙዚቃዎች እንዳሉት ነገረኝ፡፡ ከቴዲ አፍሮ ደግሞ ላምባዲና የተሰኘውን ሙዚቃ እንደሚወደው ገለጸልኝ፡፡ ስለ ድምጻዊው እያንዳንዱን መረጃ እንደሚከታተል ጭምር ሲገልጽልኝ በቅርቡ ለኮራ ሽልማት መታጨቱንም በመንገር ነበር፡፡
ኬንያዊው ዲጄ ኤም ምሽት ላይ ላምባዲናን እንደሚያጫውት ቃል በመግባት እንድሰማው ጋበዘኝ፡፡ እኔ ግን ምሽቱን አዲስ አበባ ለመምጣት ናይሮቢ ነበርኩ፡፡ ላምባዲና ግን ከናይቫሻ ከተማ ሲለቀቅ ይሰማኛል፡፡ .
አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላም ይኸው ላምባዲና ከአፌ አልጠፋ ብሎኛል፡፡ እውነትም እንዴት ያለ ሀይል ያለው ሙዚቃ ነው!
……. …….. …….
“ኩራዜ ልክ እንደ እማዬ
አንቺ ነሽ ላምባ ዲናዬ”

የቴዲ አፍሮ “ላምባዲና” ከኢትዮጵያ..ርዋንዳ…ኬንያ …..(ቆንጅት ተሾመ)

| Uncategorized |
About The Author
-