kal
ህዝበ ሙስሊሙ ለተንኮለኞች ሴራ ሳይበገር አንድነቱን አጠንክሮ፣ አመለካከቱን አቻችሎ ሰላማዊ የመብት ትግሉን መቀጠል ይኖርበታል!
በአንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢ ታህሳስ 01/2008 የደረሰው የቦንብ ጥቃት የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ትኩረት እንዲሰጠው፣ ድርጊቱም በገለልተኛ አካላት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን!
አርብ ታህሳስ 15/2008 /አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሕገመንግስታዊ የመብት ጥያቄያችንን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማቅረባችን ይታወቃል። ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን እና ፍትሃዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄውን በሀሰት በመፈረጅ ሰላማዊ ሂደቱን ለመቀልበስ ተደጋጋሚ ጥረት ተደርጓል። የህዝበ ሙስሊሙን የፍትህ ጥያቄን ለማጠልሸት እና በመካከሉ ልዩነትን ለመፍጠር የተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሄ ለማፈላለግ ሕዝብ በወከለን መሰረት በመንቀሳቀሳችን ወንጀለኛነት እና የረጅም እስር ፍርድ እንዲወሰን ተደርጓል። ይህም ሁሉ ሆኖም የሙስሊሙን አንድነት መስበርም ሳይቻል ቀርቶ ለመብቱ መከበር የሚያደርገውን ትግል በተጠናከረ መልኩ እየቀጠለ ባለበት ወቅት እጅግ ጸያፍ የሆነ የቦምብ ጥቃት በእምነት ቤታችን ቅጥር ግቢ ውስጥ መሰንዘሩ እጅግ ያሳዘነን ክስተት ነው።

የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊ የትግል ሂደት መንገድ ሊያስቱ እንደሚሞክሩ ደጋግመን ስናስጠነቅቅ ቆይተናል። የሸፍጥ ጥቃቶችን በስውር በመፈጸም ፓለቲካዊ ጥቅም የሚያስገኙ እርምጃዎችን ለመውሰድ የማመቻቸት ተግባር በተለያዩ ሀገሮች የምናየው ክስተት ነው። በሰላማዊ የትግል ሂደታችንም በተለያየ ጊዜ የተረዳነውና ያጋጠመንም ነው። ሆኖም ግን ሙስሊሙ ህብረተሰብ የመከላከል ስራዎች ላይ በልዩ ትኩረት በመስራቱ ሰላማዊ ሂደታችን ለፓለቲካ ግብዓት እንዳይውል እድሉን ነፍጓቸው ቆይቷል። እንግዲህ በአንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ታህሳስ 01/2008 የደረሰው የቦንብ ጥቃት ቀደም ብለን እንደ ህዝብ ገምተን ስንከላከለው፣ መንግስትም የሀይማኖት ተቋማትን በተለይም የመስጂዶችን ደህንነት ለመጠበቅ በኩል ያለበትን ሀላፊነት በትክክል እንዲወጣ ስናስጠነቅቅበት የቆየነው እንጂ ሌላ አይደለም።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ፍትሃዊና ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ለመቀጠል ዳግም ቃል እየተጋባ ባለበት በአሁኑ ወቅት እና አማኞች የፈጣሪያቸውን ግደታ ለመወጣት በተሰባሰቡበት ቦታና ሰዓት የቦንብ ጥቃት ማድረስ በእርግጥም የሙስሊሙን ሰላማዊ ሂደት ለማጠልሸት፣ የትግል ወኔውን ለመስበር፣ አንድነቱን ለመረበሽ ዛሬም የማይፈነቀል ድንጋይ እንደማይኖር የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ በመነሳት በቀጣይም በመስጊዶች ብቻ ሳይወሰን በክርስትና እና በሌሎች የአምልኮ ቦታዎችም ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶችን በማድረስ በተለያዩ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን መካከል ቅራኔን ለመፍጠር ሙከራዎች እንደሚደረጉ መገመት ከእውነታ የራቀ አይሆንም። በዚህ አይነት የተንኮለኞች ሴራ አገራችን እና ህዝባችን አደገኛ ወደ ሆነ አቅጣጫ እንዲመሩ አንፈቅድም። በመሆኑም ጉዳዩ የዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲቸረው እና ይህ እኩይ ተግባር በገለልተኛ አካል ይጣራ ዘንድ ሀገር እና ወገን ወዳድ የሆኑ ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ አጥብቀን እንጠይቃለን። በደረሰው ጥቃት ለተጎዱት ወገኖቻችን፣ እንዲሁም ለመላው ሙስሊም ህብረተሰብ እና ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሁኔታው የተሰማንን ሀዘን እንገልጻለን። ህዝበ ሙስሊሙም በፍንዳታው ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞቹ እና ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ እና ከጎናቸው በመቆም አጋርነቱን፣ አንድነቱን እና ከምንም በላይ የትኛውም አይነት ሴራ የማይበግረውን ከፈጣሪው በተዘረጋ የእምነት ገመድ ላይ ያለውን የአንድነት ትስስር በተግባር ሊያሳይ ይገባል።

የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄያች ፍትሀዊ ናቸው፡፡ ሂደቱም ሰላማዊ ነው። በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ጥርጣሬን ለማስፈን፣ ክፍፍልን በማምጣት እርስ በርሱ ለማጋጨት የሚፈጸም የትኛውም ደባ የከሸፈ ከንቱ ጥረት ነው። ህዝባችን በዚህ እና መሰል ሴራዎች ሳይበገር አንድነቱን ጠብቆ፣ አመለካከቱን አቻችሎ ሰላማዊ የመብት ትግሉን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን።

አገራችን ያለችበትን ተጫባጭ የታሪክ ፈታኝ ምእራፍ በመረዳት ህብረተሰባችን ያለአንዳች የብሄር፣ የዘር፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ለፍትህ እና ለሕግ የበላይነት በመቆም ዜጎቿ በሰላም ተሳስበን የምንኖርባት ሀገር ትሆንልን ዘንድ ጠንክረን መታገል ይኖርብናል። ለዚህ ስኬት ከጥረታችን ባሻገር ሁላችንም ፈጣሪያችንን በጽኑ እንለምን። በመተናነስ፣ በጸሎት፣ በሰደቃ እና በመልካም ተግባር ወደፈጣሪያችን አላህ (ሱ.ወ) መቃረብ እንደሚኖርብን ህዝባችንንም ራሳችንንም ሳናስታውስ አናልፍም!

ድል የሚከጀለው ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!

የአንዋር መስጊዱን የቦምብ ጥቃት አስመልክቶ በእስር ቤት ከሚገኙ የኮሚቴው አባላት የተሰጠ መግለጫ አርብ ታህሳስ 15/2008

| Uncategorized |
About The Author
-