ቡና በአርባ አመት ታሪኩ የመጀመሪያውን የውጪ አሰልጣኝ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መሬት ቀጥሯል፡፡ በቡና ታሪክ የውጪ አሰልጣኝ የማይታሰብ ነበር፡፡ ግን አደረጉት፡፡ የውጭ አሰልጣኝም ለመቅጠር ለምን አስፈለገ? ሌላው ሲቀጥር ታይቶ ነው ወይስ ጥናት ተደርጎበት? ቡና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለለውጥ የሚሄድ ክለብ ነው፡፡ ዋንጫን በእድገት ውስጥ የሚፈልግና አሸናፊነትን በውበት ውስጥ ለማምጣት የሚሄድ ቡድን ነው፡፡ ይሄንን ሂደት እዚሁ ሀገር በሚገኙ አሰልጣኞችና የኛን ተጫዋቾች መነሻ ባደረጉ መልኩ ለሚሰሩት ለውጥ ለማምጣት የሚሄድ ነው፡፡
ከውጪ ሀገር በመጡ አሰልጣኞች ምንም ነገር እንደማይገኝ እየታወቀ ቡና ለምን ይሄን መንገድ መረጠ? በብሄራዊ ቡድን 39 የውጪ አሰልጣኞች መጥተው ምንም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ ክለቦቻችን ከውጭ አሰልጣኝ አምጥተው መለወጥ አልቻሉም፡፡ መብራት የውጪ አሰልጣኝ ከእንግሊዝ፣ ጣሊያንና ከቡልጋሪያ አስመጣ፡፡ ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡ 1995 ካሳዬ ቡናን ይዞ መብራት የጣሊያን አሰልጣኝ ይዞ በጥሎ ማለፉ ፋይናል ተገናኝተው በውጤትም በጨዋታ ውበትም አልተመጣጠኑም፡፡ ጣሊያናዊ አሰልጣኝ ካሳዬን አድንቆት ነበር፡፡ ደደቢት ከሁለት ሀገር አልጣኝ አስመጣ፤ ግን ምንም ለውጥ ስላላመጣ አሰናበቱ፡፡

10686718_313313845519491_4852482643668475885_n
ቡና ከውጪ አሰልጣኝ ሲያስመጣ አጥንቶ ነው? ምናልባት ጊዮርጊስ ከውጪ አሰልጣኝ እያስመጣ እኛ እንዴት ?…… በሚል ስሜት ፈረንጅ አስመጥተው ሊሆኑ ይችላል፡፡ ግን ይሄንንም መመርመር ይገባል፡፡
እርግጥ ነው ጊዮርጊስ ከውጪ አሰልጣኝ እያስመጣ ነው፡፡ ከ1996 ጀምሮ ለአስራ አንድ አመት ያህል የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ትተው በውጪ አልጣኝ እየሰሩ ነው፡፡ ጊዮርጊስ በዚህ አስር አመት ውስጥ 8 ያህል ዋንጫ ወስዷል፡፡ ይሄ ሲታይ ውጤቱ የተገኘው በውጪ አሰልጣኝ ያስመስላል፡፡ ግን ነገሩን በእውቀት ሲገመገም ጊዮርጊስ በውጪ አሰልጣኝ ተጠቃሚ አልነበረም፡፡ ጊዮርጊስ ከውጪ አሰልጣኝ ከመቅጠሩ በፊት በተደጋጋሚ ዋንጫ አግኝቷል፡፡ የውጭ አሰልጣኝም ቀጥሮ ዋንጫ አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ ከውጪ አሰልጣኝ ከመቅጠሩ በፊት በሀበሻ እየሰለጠነ በኢንተርናሽናል ወድድር ደካማ ነው፡፡ ከውጪ አሰልጣኝ ቀጥሮም በኢንተርናሽናል ውጤቱ ደካማ ነው፡፡ ሴካፋን ዋንጫ እንኳን ማንሳት አልቻለም፡፡ ጊዮርጊስ ያስመጣቸውን የውጪ አሰልጣኝ ያባረረው በሀገር ውስጥ ዋንጫ እያመጡ ነው፡፡ ለምን ቢባል በውጪ ውጤት ስላላገኙ ነው፡፡ እናም የውጪ አሰልጣኞች ጊዮርጊስ በፊት የነበረውን ውጤት ነው የሚያሳዩት እንጂ የተለየ ነገር አላመጡም፡፡
እነዚህ ከውጪ የመጡት አሰልጣኞች በክለብና በብሄራዊ ምንም ውጤት አለማምጣታቸው እየታወቀ ቡና ከምን ጥናት ተነስቶ ነው የውጪ አሰልጣኝ ያስመጣው? ሌላው ጉዳይ አንዋር ምክትል ነው፡፡ ሰሞኑን እንደሰማሁት የውጪ አሰልጣኝ በመቀጠሩ አንዋር ከፈረንጁ ጥሩ ትምህርት ያገኛል መባሉ ነው፡፡ ማነው ትምህርት የሚወስደው? አንዋር አይደለም ከሰውየው የሚማረው፡፡ ፈረንጁ ነው ከአንዋር የሚማረው፡፡ አንዋር የኢትዮጵያን ተጫዋች መነሻ ባደረገ መልኩ ነው የሚያሰለጥነው፡፡ ይሄም ከሌሎች አሰልጣኞች ወጣ ባለ መልኩ ነው የሚያሰራው፡፡ ፈረንጁ ግን የተለመደውን ሌሎች አሰልጣኞቻችን የሚያሰሩትን ነው እስከዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለውጥ ያላመጣውን አሰለጣጠን ነው የሚያሰራው፡፡ ሄንን አሰለጣጠን ደግሞ አንዋር በሌሎች የሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ለረጅም ግዜ አይቶታል፡፡ ስለዚህ ከፈረንጁ የሚማረው ነገር የለም፡፡ ፈርንጁ ግን ሌላ ቦታ አይቶ የማያውቀውን ነገር አንዋር ሊያሳየውና ሊያስተምረው ይችላል፡፡
እስከዛሬ የውጪ አሰልጣኝ የሀገራችን ተጫዋች መነሻ ያደረገ ነገር አሳይተውን አያወቁም፡፡ ሁሌም አሰርተውን የሚሄዱት በተቃራኒው እኛ በሌለን ነገር ላይ ተመርኩዘው ነው፡፡ ስለዚህ ፈረንጁ ተምሮ ሊሄድ እንጂ በቡና ምንም ለውጥ ሊያመጣ አይደለም፡፡ አማካሪውን ጨምሮ የቡናን ኮሚቴ በአንድ ነገር አድነቅኩ፡፡ እስካሁን እኛ ሀገር ፈረንጅ ሲመጣ ለአራት አነሰ ቢባል ለሁለት አመት ነው የሚያስፈርሙት፡፡ ቡና ግን አንድ አመት ነው፡፡ ይሄም ጥሩ ብልጠት ነው፡፡ ካልሆነና ካላዋጣ ሳይከስሩ ቶሎ ማሰናበት ነው የሚያዋጣው፡፡ ግን አንዋር እምነት ይጣሉበት፡፡ እሱ ለያዘው ስልጠና የሚሆን ሰው እንዲመርጥ እድል ይስጡት፡፡ አንዋር ከአሰልጣኝም በላይ ለለውጥ የሚሰራ ነው፡፡ ቡና ደግሞ በለውጥ ውስጥ አንድ ነገር ለማሳየት የሚሄድ ነው፡፡

Facebooktwittergoogle_plusredditFacebooktwittergoogle_plusreddit

Category:

Uncategorized

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

four × three =